በአለም በትልቅነቱና በዝናው ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መርከብ – ታይታኒክ! ይህ መርከብ እጅግ ትልቅና በፍጹም ምንም ነገር ሊያሰጥመው አይችልም የተባለለት መርከብ ነበር፡፡ ቅጽል ስሙ፣ “የማይሰጥመው መርከብ” ነው፡፡ እንደውም ይህንን መርከብ የሰሩት ሰዎች “አምላክ እንኳ ሊያሰጥመው አይችልም” በማለት አጋንነው በድፍረት ይናገሩለት ነበር፡፡ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1912 ዓ/ም አንድ ነገር ተከሰተ፡፡
መርከቡ በጉዞ ላይ እንዳለ፣ በፊቱ የበረዶ ክምር እንዳለ ማስጠንቀቂያ ለካፒቴኑ ይደርሰዋል፡፡ ካፒቴኑ ማስጠንቀቂያውን ከቁጥርም አልከተተው፡፡ በባህር ላይ የሚገኙ የበረዶ ክምሮች (Iceberg) ጫፋቸው ትንሽ፣ ከታች በውኃው የተሸፈነው አካላቸው ግን ግዙፍ በመሆናቸው ይታወቃሉ፡፡ ይህ ካፒቴን ለስድስተኛ ጊዜ ማስጠንቀቂያው ሲመጣለት የሰጣቸው ምላሽ፣ “ቢዚ ነኝ ተውኝ” የሚል ነበር፡፡ ይህ ቃል የካፒቴኑ የመጨረሻው ቃል እንደ ነበረ ይነገራል፡፡ ብዙም ሳይቆይ ታይታኒክ በደረሰበት የግጭት አደጋ ለመስጠም በቃ፡፡ የብዙ ሰዎች ሕይወት አለፈ፣ ብዙ ክስረትና ሃፍረት ደረሰ – በአንድ ሰው እስከሞት በሆነ ቢዚነት!!!
ቀናችንን የምናሳልፈው በምን ላይ ነው? በአስፈላጊው ወይስ በአጣዳፊው? ቀኑ አልቆ ማታ ወደ ቤታችን ስንገባ፣ መለስ ብለን ውሎአችንን ስናስበው ብዙውን ጊዜአችንን የወሰደው ነገር ምን ያህል ቁም ነገር ያለው ጉዳይ ነው? ከአስፈላጊው ጉዳይ ላይ ትኩረታችንን የወሰደው አጣዳፊውና አንገብጋቢው ነገር ምንድን ነው? የተግባር “ቆጠራ” እና “ቁጥጥር” ካላደረግን ያልታሰበና የቀስ በቀስ ሞት መሞታችን አይቀርም – ለሕይወትና ለእድገት የሚሆኑትን ትተን ለጊዜአዊ ስሜት ግለት በሆነው እንወሰዳለንና፡፡ ብዙ ሰዎች “ቢዚ” ናቸው – እስከሞት ድረስ “ቢዚ”!
ምንም “ቢዚ” ብትሆን . . .
• ለቤተሰብህ ጊዜ እስከምታጣ ድረስ “ቢዚ” አትሁን!
• ለትዳር አጋርህ ጊዜ እስከምታጣ ድረስ “ቢዚ” አትሁን!
• ጤንነትህን ለመንከባከብ ጊዜ እስከምታጣ ድረስ “ቢዚ” አትሁን!
• የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድግ ጊዜ እስከምታጣ ድረስ “ቢዚ” አትሁን!
• ለማንበብና አእምሮህን ለመመገብ ጊዜ እስከምታጣ ድረስ “ቢዚ” አትሁን!
• ለብቻህ ሆነህ ሩጫህን ለመገምገም ጊዜ እስከምታጣ ድረስ “ቢዚ” አትሁን!
• ከአንተ የተሻሉ ሰዎች የሚሰጡህን ምክር ለመስማት ጊዜ እስከምታጣ ድረስ “ቢዚ” አትሁን!
አስተያየት ያስቀምጡ