“ፍርሀት በሚይዘኝ ጊዜ፣ መታመኔን በአንተ ላይ አደርጋለሁ።“…
ቦታው ኢንግሊዝ ነው፣ ድንገት ጥይቱ እንደ ዝናብ መርከፍከፍ፣ መድፉም እንደ መብረቅ ማምባረቅ ጀመረ። ጊዜው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ነውና በአውሮፓ የትኛውም ቦታ ላይ ቢሆን እንዲህ አይነቱን ድምጽ መስማት የተለመደ ሆኗል። በዚህ ጊዜ አንድ አባትና ትንሽ ልጁ ቦምብ ከሚጥል አውሮፕላን ራስን ለመከላከል ወደ ተሰራው ምድር ቤት ውስጥ እየሮጡ ገቡ።
ከጥቂት ጊዜ በፊት የልጅቱ እናት በዚህ ጦርነት ተገድላ ነበር። አባትየውና ልጅቱ እዚያው እንደተሸሸጉ መሸ። ውጊያው ስላልረገበ እዚያው ለማደር ተገደዱ። ከበላያቸው ሞትና ጥፋት ስለነበር ትንሿ ልጅ በጣም ፈራች። እየመሸ ስለሄደ ትንሽ እንኳን ልጅቷ እንቅልፍ ቢወስዳት ብሎ በክፍሉ ውስጥ ባለው አልጋ ላይ አባትየው ልጅቱን በአንድ ጥግ ላይ አመቻችቶ ካስተኛ በኋላ እርሱ ደግሞ አንዱን ጥግ ይዞ ጋደም አለና ሻማውን አጠፋው።
ልጅቱ ለመተኛት ብትሞክርም እንቅልፍ ሊመጣላት አልቻለም። በቅርብ ጊዜ እናቷን በዚህ አይነት የተኩስ ልውውጥ ስላጣች፣ ክስተቱ ድቅን እያለ አወካት። ፍርሃት ከበባት። ጸጥ ባለውና ጥቅጥቅ ባለው ጨለማ ውስጥ ቀስ ብላ እያንሾካሾከች “አባዬ አለህ?” አለችው። “አዎን ልጄ አለሁ አይዞሽ አትፍሪ ተኚ” አላት። መልሶ ክፍሉ በጸጥታ ተዋጠ።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ጨለማው እያስፈራት፣ እንቅልፉም ይበልጡኑ እየሸሻት ስለሄደ አባቷን ጠርታ እንዲህ አለችው። “አባዬ አንድ ነገር ብቻ ልጠይቅህ፣ ፊትህን ወደኔ ነው አዙረህ የተኛኸው?” አለችው። እርሱም “አዎን ልጄ አትፍሪ ፊቴ ወደ አንቺ ነው የዞረው። አትፍሪ ተኚ” አላት። ብዙም ሳይቆይ እንቅልፍ ይዟት ጭልጥ አለ።
አንዳንዴ ሕይወት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደተጣልን ያህል አስፈሪ ትሆናለች። መራመጃ ፍንጭ እስክናጣ ድረስ ትፀልማለች፣ ትደነግዛለች። “በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ያህል ቀርቶአል” እስክንል ድረስ ተስፋ እናጣለን። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አንድ ነገር አንርሳ፣ የትኛውም የሕይወት ጨለማ እኛን ከማየት የማያግደው አምላክ አለን፤ ፊቱ ዘወትር ወደ እኛ እንደዞረ ነው።
የሁኔታዎች መደራረብ እርሱን እንዳናይ አድርጎን ይሆናል እንጂ እርሱ እኛን ከማየት ታቅቦ አያውቅም። በእጁ መዳፍ የቀረጸንን፣ እንደ ዐይኑ ብሌን የቆጠረንን አያየንም፣ አያስታውሰንም ብንል ፈጽሞ ሐሰተኛ እንሆናለን። ፍርሃት ሲዳብሰን፣ ጭንቀት ሊሰፍርብን ሲያሰፈስፍ ከመዝሙረኛው ጋር አብረን እንዲህ እንበል “ፍርሀት በሚይዘኝ ጊዜ፣ መታመኔን በአንተ ላይ አደርጋለሁ።” (መዝሙር 56፡3)።
መልካም ቀን!
አስተያየት ያስቀምጡ