“መከራህን ትረሳለህ፤ ዐልፎ እንደ ሄደ ጐርፍም ታስበዋለህ።“...
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(UN) እ.ኤ.አ በ1993 ዓ.ም በሱዳን የተከሰተውን ድርቅ እና ራብ አስከፊነት ለተቀረው የዓለም ሕዝብ የሚያስረዳለት ጥሩ ፎቶ ይፈልግ ነበር። ለዚህም ሥራ ባለሙያዎችን አወዳደረ፣ ኬቨን ካርተር አሸነፈ። ኬቨን ካርተር ነጭ ደቡብ አፍሪካዊ ሲሆን፣ የተሳካለት የፎቶ ጋዜጠኛ (ፎቶ ጆርናሊስት) ነበር።
ራቡ በጣም በጸናባት በአዮድ መንደር ውስጥ እየተዘዋወረ ፎቶ ያነሳ ጀመር። ከመንደሯ አለፍ እንዳለ ዛጎል አንገቱ ላይ ያጠለቀ፣ ራብ የደቆሰው ልጅ አጥንቶቹ እየታዩ መሬት ላይ ተደፍቶ አየ። ትንሽ ራቅ ብሎ ደግሞ ገዘፍ ያለ ጥንብ አንሳ ልጁን ለመብላት እየተመኘ የጎሪጥ ያያል። ኬቨን ጊዜ ሳያጠፋ ክስተቱን ፈጠን ብሎ ቀረጸው። ልጁ አቅራቢያው ወደሚገኝ የእርዳታ ጣቢያ ለመሄድ እየሞከረ ነበር፣ ነገር ግን አቅም ስላጣ እዚያው ኩርትም ብሎ ቀርቷል። ኬቨን ጥንብ አንሳውን እሽ! እሽ! ብሎ ለማባረር ሞከር አድርጎ ሌላ ፎቶ ለማንሳት ጉዞውን ቀጠለ።
እንደጨረሰ የቀረጻቸውን ፎቶዎች ለ’UN’ አስረከበ። ይህች ፎቶ ግን አይደለም የተባበሩትን መንግስታት ድርጅት፣ የዓለምን ሕዝብ ሁሉ አነጋጋሪ ሆነች፣ ተደነቀለት፣ ተጨበጨበለት። የዓመቱ ምርጥ ፎቶ ተብሎ ‘የፑሊትዘር አዋርድ‘ ተሸለመበት። ከውዳሴው ጎን ለጎን ግን ያገኘው ሰው ሁሉ አንድ ጥያቄ ያቀርብለት ጀመር፣
“ያንን መሬት ላይ ተደፍቶ የነበረውን ህጻን ምን አደረክለት?!”
እርሱም ይመልሳል፣ “ጥንብ አንሳውን አባረርኩለት!”
ጥያቄው በተደጋገመ ቁጥር ወቀሳ እና ጸጸት አእምሮው ላይ ቤታቸውን ሰሩ። “ያ ህጻን ምን ሆኖ ይሆን?”፣ “ጥንብ አንሳው በላው?፣ ወይስ እንደ ራበው እዚያው አቃስቶ ሞተ?”፣ “ለምን አልረዳሁትም?”፣ “ለምን አቅፌ ወደ መጠለያው አልወሰድኩትም?” የሚሉ የጸጸት ጥያቄዎች እየተፈራረቁ ቀጠቀጡት። ከዚህም የተነሳ ሽልማቱን በተቀበለ በ3ኛው ወር ሕይወቱን አጠፋ።
❝መጪውን ቀን የተሻለ ለማድረግ የማይጠቅም ጸጸት ሁሉ ምንጩ ከዚያ ከክፉው ነው። ቃሉ እንደሚለው “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ሐዘን ወደ ድነት ለሚያደርስ ንስሓ ያበቃል፤ ጸጸትም የለበትም። ዓለማዊ ሐዘን ግን ለሞት ያበቃል።” (2ኛ ቆሮንቶስ 7፡10)፤ ባለፈው ዘመናችን ያበላሸናቸው ነገሮች ይኖራሉ፣ አሉም። ግን እነርሱን ነገን ለማስዋቢያ፣ ለመካሻ እንጂ ለማጨለሚያ ማዋል የለብንም። ጌታ ቀን የሚጨምርልን ያጣመምነውን እንድናቃና፣ የጣልነውን እንድናነሳ፣ የሰበርነውን እንድንጠግን እንጂ የበለጠ እንድናበላሽና በክፋት እንድንሰለጥን አይደለም።❞
በሚገርም ሁኔታ ከ 18 ዓመት በኋላ በዚያ ፎቶ ላይ የሚገኘው ልጅ አባት በ 2011 ዓ.ም ጋዜጠኞች አግኝተው አናግረውት ነበር። ልጁ ወደ እርዳታ ጣቢያ እንደገባና በሌላ ህመም እስኪሞት ድረስ ተጨማሪ 14 ዓመታትን እንደኖረ መሰከረ። ❝ያስቆጫል!!! ምናለበት ኬቨን ለውሳኔ ባይቸኩል! በጸጸቱ ሰይፍ ከመሰየፍ ይልቅ ቢሳልበት፣ በቁጭቱ እሳት ከመበላት ይልቅ ቢበስልበት! በወቀሳው ድንጋይ ከመጨፍለቅ ይልቅ ቢሞረድበት! ዛሬም ብዙዎች በኬቨን መንገድ ለመሄድ ሲመርጡ ይታያል፤ ይህ አካሄድ ለዚያ ለነፍሳት ጠላት ድርብ ድል የሚሰጥ የይሁዳ መንገድ ነው!
እንድንሻሻልና እንድንታረም የማያደርገን ጸጸት ሁሉ ምንጭ ሰይጣን ነው። ዘወትር እየተመላለሰ አእምሮህን የሚቆነጥጥ፣ ቀና ልትል ስትል የሚያጎብጥ፣ ልትራመድ ስትሞክር የሚሸመቅቅ ክስ ካለብህ ከእግዚአብሔር እንዳልሆነ ስነግርህ ያለ ፍርሃት አፌን ሞልቼ ነው!
ልከኛው መንገድ የጴጥሮስ ነው! የከሃዲነት ጅራፍ ቢገርፈው፣ በንስኃ ኃይል አለፈው።
ያ ችኩሉ፣
ፍጥን ፍጥን ባዩ፣
እዩኝ እዩኝ ባዩ፣
አለሁ አለሁ ባዩ፤ ከጸጸት በኋላ ግን ሌላ ሰው ሆኖ መጣ። ሰከነ፣ በረደ፣ ተሞረደ! በንስኃ በኩል ተፈልቅቆ ወጣ። በካደበት አደባባይ መሰከረ፣ በዋሸበት አፉ የእውነት ጠበቃ ሆኖ ቆመ፣ የአምላክ ይቅር ባይነትና ቁስል ጠጋኝነት ሕያው ማሳያ ሆነ። እኛም የጌታን እጅ እስካለቀቅን ድረስ አሳፋሪ ምዕራፋችን ተዘግቶ አዲስ ብስራት ይወለዳል፣ አዲስ መንገድ ይቀደዳል። ከልባችን ቁስል እንድናለን፣ እንጠገናለን፤ “መከራህን ትረሳለህ፤ ዐልፎ እንደ ሄደ ጐርፍም ታስበዋለህ።” (ኢዮብ 11፡16) የሚለው የተስፋ ቃል ያገኘናል።❞
እንደ ኬቨን በውሳኔያችን የምንጎዳ
ነጋችንን የምናበላሽ አያድርገን።
አሜን‼
አስተያየት ያስቀምጡ