ሁላችንም ዘውትራዊ የሆነ የልብ መሻት አለን። አንደኛውን ቀን ሸኝተን ሌላኛውን ስንቀበል ከትላንቱ ይልቅ ምኞታችን ላይ እንቀርባለን። ጣፋጭ የሆነችው የማለዳ ፀሃይ ይህንን መልካም ዜና በየጠዋቱ ታበስረናለች። ነገር ግን ሰርክ እንዳሰብነው ሁኔታዎች ላይሄዱ ይችላሉና ቀን ሲጎድል ልብ ይከዳል። ስሜት ከራስ ጋር ተፋቶ ባዶነት ይነግሳል። የሌሊቱን ማለቅ የምታበስረው የፀሃዮ ፍንጣቂ ውስጣችን ያለውን ድቅድቅ ጨለማ አጉልቶ የሚያሳይ ስለሚመስለን እንፈራለን።
በሁኔታዎች ላይ ተስፋ ማድረግ መጨረሻው ሁልጊዜ ያማረ ላይሆን ይችላል። እነዚህ የተደገፍንባቸው ነገሮች ፅኑ መሰረት የላቸውምና አንድ ቀን መውደቃቸው አይቀሬ ነው። ነገሩን ደግሞ ይበልጥ የከፋ የሚያደርገው ከእነርሱ ጋር እኛኑ ይዘው መሬት ላይ መጣላቸው ነው። የከፍታችን ምክንያት ብለን ተስፋ ያደረግነው ነገር ከስፍራው ባለመኖሩ መገኛችንን ታች ያደርገዋል።
ይህ ሀሳብ አንድን ጥያቄ እንድናውጠነጥን ዕድሉን ይሰጠናል፦ “ሁልጊዜ ተስፋ የማደርገው ነገር ይኖር ይሆን?” ምላሹ እንደ መታደል ሆኖ “አዎን!” የሚል ይሆናል። እግዚአብሔር ዘውትር ተስፋ የሚጣልበት ታማኝ አምላክ ነው። እርሱ ከጊዜ ውጪ ሆኖ ነገር ግን በጊዜ ውስጥ ስለሚሰራ ከሁኔታዎች ሁሉ በላይ ነው። ለዚህ ነው ባለ ቅኔው እንደዚህ ሲል የሚደመጠው፦ “እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።” (መዝ 27፥14) የተስፋችን መሰረት ይወድቃል ብለን የማንሰጋበት ፅኑ ዐለት ነው። ስለዚህ ሰርክ እግዚአብሔርን ተስፋ እናድርግ። ይህም ይሁን ምስክርነታችን፦ “እኔ ግን ሁልጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፥ በምስጋናህም ሁሉ ላይ እጨምራለሁ።” (መዝ 71፥14)
🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ዘመናቶቼን ስላሳመርክልኝ አከብርሃለሁ። ዘውትር አንተን ተስፋ ማድረግን አስተምረኝ። አሜን።
አስተያየት ያስቀምጡ