“የእግዚአብሔር ቤት” የእግዚአብሔርን መገኘት የሚያመለከት ሲሆን መዝሙረኛው በእግዚአብሔር መገኘት ውስጥ መሆንን ከምንም በላይ እንደሚመርጥ ደጋግሞ ይዘምራል። እኛስ ከሥፍራዎች ሁሉ የምንመርጠው ስፍራ ምን ይሆን? ይህንን ጥያቄ በልባችን ይዘን የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመልከት።
1 የምንመርጠው ሥፍራ
መዝሙረኛው ከምንም ነገር በላይ አስበልጦ የመረጠው ነገር ቢኖር በእግዚአብሔር ቤት፣ በእርሱ መገኘት ውስጥ መኖርን እንደሆነ እነዚህ ጥቅሶች ይመሰክራሉ።
“እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤
እርሷንም እሻለሁ፤
ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣
በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣
የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣
በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው።” መዝ 27፡ 4
“በሌላ ስፍራ ሺሕ ቀን ከመኖር፣
በአደባባይህ አንዲት ቀን መዋል ይሻላል፤
በክፉዎች ድንኳን ከመቀመጥ ይልቅ፣
በአምላኬ ቤት ደጅ መቆም እመርጣለሁ።” 84: 10
2 የምንለመልምበት ሥፍራ
የእግዚአብሔር ቤት ሥር ሰደን የምንለመልምበት፣ ሁልጊዜ ፍሬ እያፈራን የምንኖርበት እውነተኛውን ስኬት ልንቀዳጅ የምንችልበት ብቸኛው ሥፍራ ነው። ይህንን አስመልክቶ መዝሙረኛው እንዲህ በማለት ይዘምራል፦
“ጻድቃን እንደ ዘንባባ ይንሰራፋሉ፤
እንደ ሊባኖስ ዝግባም ይንዠረገጋሉ።
በእግዚአብሔር ቤት ተተክለዋል፤
በአምላካችንም አደባባይ ይንሰራፋሉ።
ባረጁ ጊዜ እንኳ ያፈራሉ፤
እንደ ለመለሙና እንደ ጠነከሩም ይኖራሉ።
“እግዚአብሔር ትክክለኛ ነው፤
እርሱ ዐለቴ ነው፤ በእርሱ ዘንድ እንከን የለም” ይላሉ።” መዝ 92፡ 12-15
3 የምንደሰትበት ሥፍራ
የእግዚአብሔር ቤት በእውነተኛ ደስታ ተሞልተን እርሱን በማመስገን ሥፍራ ነው።
መዝሙረኛው በእግዚአብሔር ቤት፣ በእርሱ መገኘት ውስጥ ያለውን ደስታ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦
“በአንተ ዘንድ የደስታ ሙላት፣
በቀኝህም የዘላለም ፍሥሓ አለ።” መዝ 16:11
ለዚህም ነው “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” ያለው ። (መዝ 122:1)
አባት ሆይ እኛም የአንተን ቤት፣ መገኛህን ከምንም አስበልጠን የምንመርጠው ስፍራ እንዲሆንልን፣ በዚያም ተተክለን ሁሌ እንድንለመልም፣ በአንተ ዘንድ ያለው ደስታም ልባችንን እንዲሞላው በጸጋህ እርዳን። አሜን።
መልካም ሰንበት በቤቱ ላላችሁት
ከቤቱ ውጭ ላላችሁትም መልካም በሰንበት የመባከን ጊዜ ይሁንላችሁ።
አስተያየት ያስቀምጡ