ብርሃን ስፍራውን ሲለቅ ጨለማ እንደሚተካ

Published by

on

ብርሃን ስፍራውን ሲለቅ ጨለማ እንደሚተካ እምነታችን ሲደበዝዝ ፍርሃታችንም እየደመቀ ይሄዳል። በመሆኑም የፍርሃትን ጨለማ ለመግፈፍ አማራጭ የሌለው መፍትሔ የእምነታችን ብርሃን እንዲጨምር ማድረግ ነው። ታዲያ እምነታችን እየደመቀ እንዲሄድ መዝሙረኛው የፍርሃት ጨለማ በከበበው ጊዜ ያደረገውን እኛም ልንለማመድ ይገባል።

1 ወደ ኋላ ዘወር ብለን እግዚአብሔር ያደረገልንን ማሰብ

“በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤
እግዚአብሔርም መለሰልኝ፤ ከመጠበብም አወጣኝ።” መዝ 118:5
በእርግጥም አምላካችን በጨነቀን ጊዜ ስንጠራው ችላ የሚለን ሳይሆን ስለ እኛ የሚገደው፣ ከእኛ በላይ ለእኛ የሚያስብልን መልካም አምላክ ነውና ይመልስልናል። እንዴት ከዚህ በፊት እንደረዳን ማሰባችን አሁን ላይ ለገጠመን ማንኛውም አይነት ከባድ ሁኔታ በእምነት እንደገና ወደ እርሱ እንድንቀርብ አቅም ይሆነናል።

2 አሁንም አምላካችን ከእኛ ጋር እንዳለ ማስተዋል

“እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?”
ቁ 6
ከዚህ ቀደም ስንጨነቅ ደርሶ የታደገን አምላክ ዛሬም ከእኛ ጋር እንዳለ ማወቅ ሌላው የፍርሃትን ጨለማ ከእኛ የምናርቅበት ወሳኝ እርምጃ ነው። አምላካችን መቼም ቢሆን ላይተወን ቃል ገብቶልናል። እርሱ ከእኛ ጋር ካለ ደግሞ በሚያስፈራን ነገር ሁሉ ላይ ስልጣን ስላለው ልባችን በድፍረት ይሞላል።

“ምክንያቱም እግዚአብሔር፣
“ከቶ አልተውህም፤
በፍጹም አልጥልህም” ብሏል።
ስለዚህ በሙሉ ልብ፣
“ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም፤
ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንላለን።” ዕብ 13፡ 5፣ 6

3 ፍጻሜያችን በድል እንደሚጠናቀቅ ማወጅ

“ይረዳኝ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው፤ የጠላቶቼንም ውድቀት አያለሁ። 5-7
ምንም እንኳን በእግዚአብሔር ላይ በመደገፋችን ችግሮቻችንን ወዲያውኑ ዞር ባይሉም፣ አምላካችን በራሱ ጊዜና መንገድ ያስወግዳቸዋል። ይህንን በማሰብ እኛም እንደ ጳውሎስ እንዲህ ልንል ይገባል፦
‘የአሁኑ ዘመን ሥቃያችን ወደ ፊት ሊገለጥ ካለው፣ ለእኛ ከተጠበቀልን ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም እንዳይደለ እቈጥራለሁ። ‘ ሮሜ 8:18

አባት ሆይ፣ እኛም የፍርሃት ጨለማ ሲከበን፣ ወደ ኋላ ዘወር ብለን እንዴት እዚህ እንዳደረስኸን እንድናስብ፣ አሁም ከእኛ ጋር እንዳለህ እንድናስተውል፣ ደግሞም ወደፊት ካንተ የተነሳ ፍጻሜያችን በድል እንደሚጠናቀቅ ማወጅ እንድንችል በጸጋህ እርዳን። አሜን።

አስተያየት ያስቀምጡ

Discover more from Edudream Family Community

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading