ወደቅሁኝ ሲለኝ አልደገፍኩትም፣ እራስ ወዳድነቴን አሳየውት፣ እርቦት አይቸው ከምሰጠው ይልቅ፣ ከንፈሬን መጠጥሁኝ። ኪሴ ሆዳም ሆኖ ምንም የለኝም ተምሯል፣ ከትናንትናው ዛሬ የተሻለ አቅም ቢኖረውም የለኝምን ማለትን ስለለመደ አሁንም የለውም። አይ ሰው ሰውነቴ፣ ለሰዉነቴ ያልሆነ፣ ሰውነትን ትቶ ጭካኔን የተማረ፣ የህሊናን ጥያቄ እንደሚመቸው የሚመልሥ፣ በራስ ወዳድነት ለዘመናት የሚገዛ፣ ህሊና ተጨፍልቆ ሥልጣኑን ተቀምቶ በሆድና በሥሥታም ስጋ ከተገዛ፣ ከእለት ከሚጠቀመው ተርፎት፣ የተቸገረውን “ዱዴ” የለኝም ካለ ያኔ በቃ ሰውነት አከተመ። ሰው ሆኖ ሰውን መደገፍ የለም ህሊና ተቀይሮ እራስ ወዳድነት ከተተካ። ወንድሜ! አትዘንጋ ሰው ላንተ በደከምክ ጊዜ ምርኩዝህ ነው፣ በተቸገርክ ጊዜ ሀሳብህን ተካፋይ ነው። ቀን ተቀያሪ፣ ከዛፍ የወጣ ወራጅ ሥለሆነ፣ስትወጣ የረገጥከው ስትወርድ እንዳታጠው፣ በአለህ ጊዜ የለለውን ሳትረሳ አስታውሰው፣ ተመርተህ በህሊናህ ዳኛ።
አስተያየት ያስቀምጡ